2176 0906570000 tradeunion@cbe.com.et

News

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች ማህበር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተላለፈ መልዕክት

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሳለፈው 80 ዓመት በዕድሜው ቀላል የማይባል ውጣውረድ አሳልፎ ከተግዳቱም እየተማረ አሁን ላለበት ቁመና መድረሱ ግልፅ ነው። ባንካችን ሀገርን ተሸክመው ለሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ ከሆኑን ጥቂት ድርጅቶች በቀዳሚነት የሚጠቀስ መሆኑን መግለፅ አይደለም ለሰራተኛው ለሌላ ማህበረሰብ ለቀባሪ ከማርዳት የሚተናነስ አይሆንም። ይህንን የሀገር ዋልታ የሆነን ባንክ ማንኛውም አካል ለራሱ ሲል ሊጠብቀው እንደሚገባ እውን ነው። ነገር ግን አንዳንድ አካላት ባንኩ የራስ መሆኑን ካለመረዳት አልያም ሆን ተብሎ በሚመስል የማደናገሪያ ሀሳቦች በተለያየ ጊዜያት አጋጣሚውን በመጠቀም ሲያነሱና ሲጥሉ ተመልክተናል። ባንኩ ግን የተፈጠሩ ተግዳሮቶችን እያለፈ አሁን ላለበት ደረጃ ደርሷል፤ ወደፊትም ከተግዳሮቱ እየተማረ ለሀገር ዋልታ እንደሆነ ወደፊት መጓዙን ይቀጥላል። በመሆኑም አርብ ሌሊት 06/07/2016 ዓ.ም የተፈጠረውም ክስተት አንዳንድ አካላት ሆን ብለው በአሉታዊ እንደሚገልፁት ሳይሆን ከትክክለኛ አካላትም ይሁን በአካል የሚመለከተውን በማነጋገር በሚገለፀው ልክ አለመሆኑን ተረድተናል። በመሆኑም ሰራተኛውም በአሉታዊ ጉዳዩን ከሚያነሱት ሳይሆን ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ከሆኑ አካላት በቅርበት በመከታተል ከማደናገሪያ ሀሳቦች እራሱን ከማራቅ በተጨማሪ ለደንበኛው እውነታውን የማስረዳት ኃላፊነት አለበት። የደንበኛ ሂሳብ እንደተመዘበረ የሚገልፅበት መንገድ ፈጽሞ የተሳሳተ መሆኑን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ከማስረዳት ባሻገር የምንሰጠው አገልግሎት ደንበኛውን በሚያረካ እና ከዚህ ቀደሙ በእጅጉ የላቀ ሊሆን እንደሚገባ እናምናለን። ክስተቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሀገር ገንዘብ መሆኑን ካለመረዳት አልያም ሆን ተብሎ ለዚያውም አነሰም በዛ ተማረ ከሚባለው አካል በአብዛኛው ድርጊቱ የተፈፀመ መሆኑን ስንመለከት በከፍተኛ ሁኔታ እንደ ማህበር ማዘናችንን እንገልፃለን። ሁሉም የባንኩ ሰራተኛ በተለያዩ ሚዲያዎች ይሰራጩ የነበሩ አሉታዊ አስተያየቶችን ለመቀልበስ በሚያስችል መልኩ የሀገር ዋልታነቱን አጉልቶ ለማሳየት ከመጣርም ባሻገር የስራ ሰዓትን ሳይጠብቅ የዕረፍት ቀኑን ሁሉ በመጠቀም ላበረከታችሁ በጎ አስተዋፅኦ ከፍያለ ምስጋናችንን እያቀረብን በቀጣይ የደንበኞችን አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ በማዘመን ሁሉም የሚተማመኑበት ባንክ መሆኑን ማስመስከር ይገባናል። የባንካችን የማኔጅመንት አካላት ችግሩ በተፈጠረ በሰዓታት ውስጥ ክፍተቱን በመለየትና ደንበኛው አላስፈላጊ መጉላላት ውስጥ እንዳይገባ አፋጣኝ መፍትሔ በመስጠት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንዲገባ ማድረጉ ስንመለከት የባንካችንን አንጋፋነት ያስመሰከረ ተግባር በመሆኑ ማህበራችን ዕውቅና የሚሰጠው ተግባር ሆኖ ሠራተኛው ምንጊዜም ከባንኩ ጎን በመሆን በጊዜ አጋጣሚ የተጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት የወደፊት ግስጋሴያችንን ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናችን እንገልፃለን። በመጨረሻም በቀጣይም ባንካችን ሚያስተላልፈውን አቅጣጫ በመቀበል እና ወደ ተግባር በመቀየር ሁሉም በያለበት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አደራ ለመስጠት እንወዳለን። ሥራ አስፈፃሚ!

0 Comments

Leave A Comment

Get In Touch

2176

tradeunion@cbe.com.et

0906570000